የ“ቀለም” አብዮት ናፍቆት!

1

የ“ቀለም” አብዮት ናፍቆት!
(ተመስገን ደሳለኝ)

የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ያበሰረው የጀርመን ግንብ ሊፈርስ ሶስት ዓመታት ብቻ በቀሩበት
ከዕለታት በአንዱ ቀን፣ ቅጥ ካጣ አምባ-ገነንነቱ በተጨማሪ ሀገሪቷን የግል ርስቱ ያደረገው የፊሊፒንስ
ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርቆስ “ታሪካዊ” የሚባል ታላቅ ስህተትን ፈፀመ፤ ጠንካራ ተፎካካሪው ሊሆን
እንደሚችል ቅድመ-ግምት ተሰጥቶት የነበረውን የተቃዋሚው ቡድን መሪ ካስገደለ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ
እንዲካሄድ የፈቀደውን ምርጫ በአሳፋሪ መንገድ አጭበረበረ፡፡ ይህን ጊዜ የሕዝቡን ትዕግስት አልባነት
የተረዱና መነሻቸው ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን የሆኑ ቁጡ ወጣቶች የማኒላ ጎዳናዎችን አጥለቀለቁ፡፡ ለሶስት
ቀናት (ከየካቲት 22-25) በቆየው ሕዝባዊ ንቅናቄም ጡንቸኛውን ማርቆስ ከመንበሩ ፈነቀሉት፡፡ አመፀኞቹ
ፊሊፒናውያን በሀገሬው ባህልና የቆየ እምነት መሰረት እንቅስቃሴው ሰላማዊ መሆኑን ለመግለፅ ሲሉ
በማኒላ አውራ መንገዶች ታንክ ጠምደው ተቃውሞውን ለማክሸፍ ለተሰለፉት የሀገሪቱ ወታደሮች ቢጫ
አበባ መስጠታቸውን ተከትሎ፣ አመፁ “ቢጫ አብዮት” የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ ይህ ሁነትም ጥቂት
ዓመታት ዘግይተው በምስራቅ አውሮፓ ለተቀጣጠሉ አብዮቶች በቀለም መሰየም መነሻ መሆን መቻሉን በጉዳዩ ዙሪያ የተዘጋጁ የታሪክ
መዛግብት ያወሳሉ፡፡ በ1990ዎቹ አጋማሽ በዚህ ክፍለ-አህጉር የተደረጉት ህዝባዊ አመፆች፣ የተለያዩ ቀለማትን እንደየሀገራቱ ባሕልና
ወግ በትእምርትነት መጠቀም መጀመራቸውም የሚያስረግጠው ይህንኑ እውነታ ነው፡፡

በአናቱም የኢራኑ የ2002ቱ “አረንጓዴ” አብዮት፣ የተቃውሞ መሪው ሆስኒ ሞሳቪ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የተጠቀመበት ቀለም በመሆኑ
ሲመረጥ፤ የቅርቡ የግብፅ አብዮትም በጥንታዊቷ የፈርኦን ምድር ልማድ፡- ትንሳኤን፣ ህይወትንና ፀሐይን በተምሳሌትነት በያዘው
“ሎተስ” በተባለ አበባ እንዲሰየም በአብዮተኞቹ ተመርጧል (የድህረ-ሙባረክ ግብፅን ወደጥንት ታላቅነቷ የመመለስ ግብን ይተረጎማል
በሚል)፡፡ ቀድሞ በግራ-ዘመሞች (ኮሙኒዝምን ለመመስረት) ይመራ የነበረው ጠብ-መንጃ ቅልቅሉ አብዮት ምዕራፍ ከተዘጋ በኋላ፣
በእንዲህ ያለ ፍፁም ሰላማዊ መንገድ የሚካሄዱ ንቅናቄዎች “የቀለም አብዮት” በሚል ስያሜ መጠራት መጀመራቸው ይታወቃል፡፡

የቀለም አብዮቶቹ በረከቶች
በምስራቅ አውሮፓ በአድቃቂው የማሕበረ-ሱታፌ (ሶሻሊስት) ሥርዓት ማግስት ብቅ ያሉት መሪዎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን
በመገንባት ሽግግሩን መምራት ባለመቻላቸው እና ነፃ ማሕበረሰብ ለመፍጠር የተነቃቃውን ልሂቅ ህልሞች በኃይል በማጨንገፋቸው
የቀለም አብዮቶቹ መቀስቀስ ብቸኛው የታሪክ ምርጫ ሆኗል፡፡ በመጨረሻዎቹ የኮሙኒዝም መንኮታኮት ዋዜማ እና በዚህ ክፍለ-ዘመን
መባቻ ላይ ግዙፎቹን ሥርዓታት ያፈራረሱ ማሕበረሰባዊ መነቃቃቶች (ሰላማዊ አብዮቶች) ከኮሙኒዝም ወደ ዲሞክራሲዊ አስተዳደር
መሸጋገርን ዋነኛ ዓላማ ከማድረጋቸው በተጨማሪ፣ ባተገባበር የጋራ መለዮ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ለሳምንታት ወይ ለወራት ድንኳን
ዘርግቶ በአደባባይ በመቀመጥ፤ አሊያም ለተከታታይ ቀናት ሰላማዊ ሰልፎችንና የሥራ ማቆም አድማዎችን በመምታት መንግስታዊ
ተቋማትን ማሽመድመድ… ከሞላ ጎደል መገለጫዎቻቸው ተደርገው ይወሰዳሉ፤ የምርጫ መጭበርበርን ተከትለው የሚቀሰቀሱ
መሆናቸውም ያመሳስላቸዋል፡፡ ለዚህም ከፊሊፒንሱ ‹‹ቢጫ›› እስከ ጆርጂያ ‹‹ፅጌረዳ››፤ ከካዛጊስታኑ ‹‹ሮዝ›› እስከ ዩክሬን ‹‹ብርቱካንማ››
አብዮቶች ድረስ የተመለከትናቸው የአደባባይ ተቃውሞዎች በድህረ-ምርጫ ወቅቶች መቀስቀሳቸው ማሳያ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም
ንቅናቄዎቹ በሙሉ የተመሩት በሲቪል ድርጅቶች አሊያም በወጣቶች ስብስብ መሆኑ ሌላው የሚያመሳስላቸው ባህሪይ ተደርጎ ሊጠቀስ
ይችላል፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ያየናቸው የቀለም አብዮቶች በዋናነት በመንገዱ ነፍስ-አባት ጄን ሻርፕ ‹ቅዱስ መፃህፍት› የተቃኙ
ሲሆኑ፤ በተለይም የአንሳንሱኪን ረዥም እስር ላመጣው ለ1985ቱ የበርማ እንቅስቃሴ የጻፈው ‹‹ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ›› የተሰኘ
ስራው ለታህሪር ወጣቶች ጭምር በመመሪያነት ማገልገሉ ይታወሳል፡፡ የዚህ የ86 ዓመት አዛውንት ጸሐፊ ዋነኛ ጭብጥ ‹‹ገዢዎች
የሚሰነብቱት ህዝብ እስከፈቀደ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ዜጎች የመገዛት ፈቃዳቸው ቀስ በቀስ እየቀነሰ ከሄደ አም-ባገነኖቹ መውደቃቸው
አይቀርም፡፡ ይህንንም ለማድረግ እነርሱ የሚያሸንፉበትን የብረት ትግል ከመምረጥ ይልቅ፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ብቸኛው
መንገድ ነው›› የሚል መሆኑ ለተቀባይነቱ አስተዋፅኦ ያደረገለት ይመስለኛል፡፡

በሌላ በኩል የቺኮዝሎቫኪያው የ‹‹ቬልቬት›› (ጀንትል) እና የዩጎዝላቪያው ‹‹ቡልዶዘር›› አብዮቶች በስኬታማነት ለመጠቀስ የሚበቁ
ናቸው፡፡ በህዳር ወር 1981 ዓ.ም የተከበረውን አለም አቀፍ የተማሪዎች ቀን አስመልክቶ ፕራግ ከተማ በተሰባሰቡት ተማሪዎች ላይ
ፖሊስ የወሰደው የኃይል ጭፍለቃ ያስቆጣቸው ግማሽ ሚሊየን ዜጎች ወደ ከተማይቱ አደባባይ በመትመም ያካሄዱት ‹‹የፕራግ ፀደይ››
የተሰኘ ሕዝባዊ ዓመፅ፣ በቀናት ውስጥ ነበር ኮሙኒስት ስርዓቱን ያንኮታኮተው፡፡ በርግጥ ለዚህ ዓመፅ መነሳሳት፣ አብዮቱን እንዲመራ
ከቤቱ የተጠራው ቫክላቭ ሆቬልና ጓዶች አቋቁመውት የነበረው ‹‹ቻርተር 77›› የተባለው የመብት ተሟጋች ሲቪክ ማሕበር የአንበሳውን
ድርሻ ይወስዳል፡፡ ብዙዎቹ አባላቱም ሀገሪቱ ቼክና ስሎቫክ ተብላ ለሁለት ከተከፈለች በኋላም በፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና
እንደነበራቸው ይታወሳል፡፡ ሌላኛው ‹‹አትፓር›› በተሰኘ የወጣቶች ንቅናቄ ተመርቶ አምባ-ገነኑን ስሎዶቫን ሚሎሶቪችን መመንገል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
2

የቻለው የ‹‹ቡልዶዘር›› አብዮት ተብሎ የሚጠራው ሕዝባዊ አመፅም፣ በሰላማዊነቱና በመልካም ምሳሌነቱ ከቀለም አብዮቶቹ ጋር አብሮ
ይዘከራል፡፡
የ‹‹ቀለም›› አብዮቶች እና እኛ
በምስራቅ አውሮፓ ሀገራት የቀለም አብዮቶች የተካሄዱበት አውድ፣ እንደኛይቷ ኢትዮጵያ የሽግግር ማሕበረሰቦች መሆናቸውን
ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ተመሳስሎ መኖሩን መካድ አይቻልም፡፡ በተለይም ከአረብ አገራት ይልቅ ከእነዚህኞቹ ጋር የሚያስተሳስረው
ከአርባና ሃምሳ ዓመታት በፊት የዲሞክራሲ ጥያቄ በኢትዮጵያም ተነስቶ የነበረ መሆኑ (መቼም በአረቦች ምድር ከአምስትና አስር ዓመት
ቀደም ብሎ እንዲህ አይነቱ ጥያቄ የሚታሰብ እንዳልነበረ ልብ ይሏል)፣ ሀገራችንም ሆነች ምስራቆቹ በሕብረ-ሱታፌ ሥርዓት
ማለፋቸው፣ በፖለቲካ የነቃ ማሕበረሰብ መኖሩ (በቅርቡ በዩክሬን የተመለከትነው አብዮት ዋነኛ መነሾ መንግስት ከአውሮፓ ሕብረት
ይልቅ ወደሩሲያ ማዘንበሉን በመቃወም እንደሆነ ይታወቃል)… የመሳሰሉት ተያያዥ ጭብጦች እነርሱ ያለፉበትን መንገድ መርምረን
ከጥንካሬያቸውም ሆነ ከድክመታቸው መማር እንድንችል ዕድል ይፈጥራል ብሎ መደምደሙ ማጋነን አይሆንም፡፡

የሆነው ሆኖ ስለመጪው አብዮት እንዲህ አብዝተን እንድንጨነቅ የሚያስገድደን የተጠቀሱት ሀገራትን ሕዝብ፣ ለተቃውሞ አደባባይ
ያወጧቸው ገፊ-ምክንያቶች እጅግ በከፋ መልኩ በዚህችም በእኛይቱ ሀገር ሞልተው የመትረፍረፋቸው እውነታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም
የተካሄዱት ሁለቱ አብዮቶች (የየካቲቱ እና የ83ቱ) ያልመለሷቸው በርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች ከመኖራቸው በተጨማሪ፣ ኢህአዴግ
ያነበረው ሥርዓት የዲሞክራሲ ጭፍለቃው ገደብ ማጣት እና የተሳሳተ ፖሊሲው ያስከተለው የኢኮኖሚ ድቀት ወደዚህ ጠርዝ የሚገፋ
ተጨባጭ ሀቅ ነው፡፡

በርግጥ የየካቲት 66ቱም ሆነ የግንቦት ሃያው አብዮቶች ከአውዳሚ ውጤቶቻቸው ጋር የተመጣጠነ ባይሆንም፣ የራሳቸው የሆነ በጎ
አበርክቶ እንዳላቸው አይካድም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀሰው፣ ቀዳሚው ከባሕላዊ እና ኋላቀር ንጉሳዊ አገዛዝ ወደ
ወታደራዊ የተደረገ ለውጥ ቢሆንም፣ የዘመናዊውን ስነ-መንግስታዊ ኑባሬ የመፍጠር ሙከራው አዎንታዊ ተብሎ በታሪክ መመዝገቡ
ሲሆን፤ ዳግማዊው አብዮት ደግሞ በተሻለ ሁኔታ የፓርቲ ፖለቲካን እና ሀሳብን የመግለፅ መሰል ጅማሮዎችን ቢያንስ በአዋጅ ደረጃ
መደንገጉ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ለዚህች አነስተኛ ውጤት አሰቃቂ የእርስ በእርስ ዕልቂትን የመሰለ ለትውልድ ክፍተት የዳረገ ውድ ዋጋ
መከፈሉ መቼም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ዛሬ አብዝሃው ሕዝብም አብዮትን በራሱ መተላለቅን የሚያስከትል መዓት አድርጎ
ለመውሰድ የተገደደው ከዚህ ካሳለፈው ጥቁር ታሪክ ጠበሳ ሳቢያ ነው፡፡ ግና፣ በእጅጉ ተናፋቂው ዘመነኛው የቀለም አብዮት ቀርቶ በእነ
ማርክስ አስተምህሮ የሚበየነውም ቢሆን እንኳ፣ ከሥርዓታዊ ለውጥ አምጪነቱ ባሻገር ጭቆና ላደነዘዘው ማሕበረሰብ ንቃተ-ህሊና
ወሳኝ መሆኑ እና በሀገር ጉዳይ ላይ ምን አገባኝ የሚል ሕዝብን ወደ ጠንካራ የፖለቲካ ተሳታፊነት ማድረሱን ፈፅሞ መካድ አይቻልም፡፡
የየካቲቱ አብዮት እንደ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አገላለፅ በደስታና በተስፋ ተጀምሮ፤ በሰቆቃና በፀፀት ቢደመደምም ከ66-68 ዓ.ም
መጨረሻ ድረስ ፈጥሮት የነበረው የአደባባይ ውይይትና የማሕበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ለዚህ ጭብጥ ሁነኛ ማሳያ መሆን ይችላል፡፡
በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ የአብዮትን አስፈላጊነት ጠቅሶ አስተያየት መስጠቱ የሥርዓቱ አገልጋዮችን ብቻ ሳይሆን፣ ለውጥ ፈላጊውንም
ሲያስበረግገው (አልፎ አልፎም እንደ ጥፋት መልእክተኛ ቆጥሮ እስከማውገዝ ሲያደርሰው) መስተዋሉ የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ግን
ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በምስራቅ አውሮፓም ሆነ በሰሜን አፍሪካ አገራት የተከሰቱት የዘመኑ አብዮቶች መነሻቸው አማራጭ ማጣት
እንጂ፤ እብሪት በገፋቸው አሊያም የሥልጣን ጥማት ባክለፈለፋቸው ቀስቃሾች የተካሄዱ አለመሆናቸውን ራሳቸው የንቅናቄው
ሰለባዎችም የሚክዱት እንዳልሆነ በግላጭ ይታወቃል፡፡ የሩሲያ አብዮት መሪ ቪላድሚር ኤሊች ሌኒን የትኛውም አገዛዝ እንደቀድሞ
በጭፍለቃ መቀጠል አለመቻሉ በአንድ በኩል፤ ተጨቋኞች ለተቃውሞ ማጉረምረማቸው በሌላ በኩል በተመሳሳይ ወቅት መከሰትን
‹‹አብዮታዊ ሁኔታ›› ሲል ይጠራዋል፡፡ በዚህ ንዑስ ርዕስም በኢትዮጵያ ‹‹አብዮታዊ ሁኔታ›› መኖሩን በማስረጃ አስደግፌ ለማተት
እሞክራለሁ፡፡

‹‹አብዮታዊ ሁኔታ››
በኢትዮጵያ ምድር ሕዝባዊ አብዮት አይቀሬ እንዲሆን ያስገደደው ዋነኛ ምክንያት ሁሉም የለውጥ መንገዶች እንዳያፈናፍኑ ተደርገው
በመዘጋታቸው እንጂ፤ ኢህአዴግ እንደሚወነጅለው ዘግናኙን የቀይ እና ነጭ ሽብር ታሪክ የመድገም ፍላጎት የተጠናወተው ፖለቲከኛ
አሊያም ተሟጋች ባራገበው የኑፋቄ ቅስቀሳ አለመሆኑ ከማንም የተሰወረ አይመስለኝም፡፡ በርግጥ ይህ የአብዮታዊ ግንባሩ ክስ፣ በሌሎች
መሰል ጉዳዮች በተከሰተባቸው ሀገራት እንደታየው የአመፅን ነባራዊ ማህበረ-ፖለቲካዊ መነሻ ከመቀበል ይልቅ፣ በውጭ ኃይሎች ላይ
ማሳበብን መምረጥ የተለመደ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ለአብነትም በቅርቡ ለእስር የተዳረጉትን ሶስት ጋዜጠኞች እና የዞን ዘጠኝ
ጦማሪዎችን ክስ ማየቱ በቂ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው የምስራቅ-አውሮፓ ሀገራትም ላጋጠማቸው ሕዝባዊ አብዮት፣ በዋናነት
አሜሪካንና የባለሀብቷን ጆርጅ ሶሮ ፋውንዴሽን የተባለ ተቋም በመወንጀል ይታወቃሉ፡፡ ይህንን መሰሉ አብዮት ያሰጋው ኢህአዴግም
የእነርሱን እርምጃ (ተቋሙን እስከመዝጋት መሄዳቸውን) በመኮረጅ፣ ከጥቂት ዓመት በፊት ካወጣቸው አዋጆች አንዱ መያዶችን
አዳክሞ (ከአስር በመቶ የበለጠ የውጭ እርዳታን እንዳይቀበሉ በመከልከል) በቁም የሚገድል እንደሆነ አይዘነጋም፡፡ በጊዜው ግንባሩ
ካቀረባቸው መከራከሪያዎች ይልቅ፣ አቶ መለስ ለ‹‹Famine and foreigners in Ethiopia›› ፀሐፊ ፒተር ጊል፤ በምዕራባውያን ሀገራትና
ተቋማት ድጋፍ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩትን መያዶች ‹‹የኒዮ ሊበራሊዝም እግረኛ ወታደሮችና ተለዋጭ ተቃዋሚዎች›› ሲል
መኮነኑ፣ የአዋጁን መግፍኤ አስረግጦ ይናገራል፡፡ ግና፣ ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ…›› እንዲሉ፤ ኢህአዴግ አለቅጥ አግንኖ ሀገር-ምድሩን
በደም የሚያጨቀይ ‹‹ጭራቅ›› አስመስሎ ፍርሃት ለማንበር እየሞከረበት ያለው ‹‹የቀለም አብዮት›› (colour revolution) የራሱ ንድፈ-
ሃሳብ የሌለው፣ ሠይፍ የማያማዝዝ፣ ፍፁም ሰላማዊ መሆኑ ከቶም ቢሆን ሊጠፋው አይችልም፡፡

የሆነው ሆኖ አገዛዙ ‹መሰል አብዮት በዚህች አገር እንዳይቀሰቀ›ስ በሚል ስጋት እንቅልፍ አጥቶ ሲባንን የሚያድረው እና የለውጥ
መንገዶችን በጠቅላላ ለመዝጋት ሌት ተቀን የሚዳክረው፣ የአረቡ ‹‹ፀደይ›› አብዮት የጨቋኞቹን የሰሜን አፍሪካ መሪዎች መንበር
በጥቂት ቀናት ውስጥ መገልበጡ የፈጠረበት ድንጋጤ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ በወቅቱ ነፍሱን ይማረውና መለስ ዜናዊ
3

በአደባባይ ‹‹ህዝቡ ያምፃል ብለን ሳንተኛ አናድርም›› ሲል ለማስተባበል ቢሞክርም፤ በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ በርካታ የተቃዋሚ
ፓርቲ አባላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ ተሟጋቾችን (አክቲቪስቶችን)… በዚሁ ጉዳይ ወንጅሎ እስር ቤት መክተቱ የንግግሩን አራምባ ቆቦነት
ያስረገጠ እርምጃ ነበር፡፡ በተጨማሪም የፓርቲው የግል ፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ ልሳን እንዲሆን በተገደደው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
ጣቢያ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ብቻ በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱ አብዮቶች አሉታዊ ጎን ላይ ያተኮሩ ዘገባዊ (ዶክመንተሪ)
ፊልሞች እና ‹‹የሕትመት ዳሰሳ›› በተሰኘ ፕሮግራሙ እየደጋገመ በማቅረብ አታክቶናል፤ ለወደፊቱም ይበልጥ እስኪያንገሸግሸን ድረስ ገና
ያታክተናል፡፡ በእነዚህ ፊልሞች እና ዝግጅቶች የ‹‹አረቡ ፀደይ››ንም ሆነ ‹‹የቀለም አብዮት››ን ደም አፋሳሽነት እየተደነቃቀፉ ሊያስፈራሩን
ከሞከሩ ዙምቢ ‹‹ተንታኞች›› አንስቶ፤ በስነ-ምግባር ጉድለት እስከተባረሩ ጋዜጠኞች ድረስ ተሳታፊ ቢሆኑም፣ ተጨባጩን የሀገራችንን
እውነታ የሚያስረግጥ አንዳች ሊያሳምን የሚችል ፍሬ ያለው ነገር ሲናገሩ አልተደመጡም፤ በስማ በለው የሰሜን አፍሪካውያንን ለውጥ
መሻት እና የዩክሬንን ሕዝብ ‹‹ፍሪደም ሃውስ››ን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ደርበው ከመርገም ያለፈ፡፡ በግልባጩ የአገዛዙን
‹‹ሚሊየነር ገበሬዎችን አፈራሁ››፣ ‹‹የምርጫ ሥርዓት ገነባሁ››፣ ‹‹በተከታታይ 11 በመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት አስገኘሁ››፣ ‹‹የብሔር
ብሔረሰቦችን መብት እስከ መገንጠል አስከበርኩ››፣ ‹‹ቀለበት መንገድ ሰራሁ››፣ ‹‹አባይን ልገድብ ነው››… ጂኒ ቁልቋል የሚለው ርካሽ
ፕሮፓጋንዳ መልሰው መላልሰው በማስተጋባት የለውጥ መንፈሱን ለማጠልሸት የሄዱበት ርቀት መልሶ ራሳቸውን ለትዝብትና ሀፍረት
የዳረገ ይመስለኛል፡፡

ያም ተባለ ይህ ሶስተኛው አብዮት አይቀሬ የሚሆንበት ምክንያት በሁለት ተከፍሎ የሚታይ ሲሆን፤ ይኸውም አማራጭ መንገዶች
መዘጋት እና ሕዝባዊ ቁጣ ቀስቃሽ ኩነቶች በተመሳሳይ ወቅት መከሰት የሚል ነው፡፡ እነዚህን ሁለት አንጓ ጉዳዮችም በአዲስ መስመር
ነጣጥለን፣ ተንትነን እንያቸው፡፡

የመጀመሪያው ‹‹መንገዶች መዘጋት›› ተብሎ የተገለፀው የዜጎችን በምርጫ ፖለቲካ እምነት ማጣት፣ የተቋማት ነፃነት መጨፍለቅ፣
የሕግ-የበላይነት መሻርን ጨምሮ በጥቅሉ በሕገ-መንግስቱ የተደነገገው የሥርዓት መቀየሪያ መንገድ መብት መገርሰስን ይወክላል፡፡ ይህ
ኩነትም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ለመከሰቱ አብይ ማስረጃ ሆኖ የሚጠቀሰው፣ በቀደሙት አራት ምርጫዎች ገዥው-ፓርቲ በማጭበርበር እና
ኃይል በመጠቀም አሸናፊነቱን ማወጁ ነው፡፡

በሁለተኛነት ‹‹ቁጣ ቀስቀሽ ኩነቶች›› በሚል የጠቀስኩት ደግሞ ከሞላ ጎደል በሚከተሉት ችግሮች ይገለጣል፡- ስርዓቱ ከእነአስከፊው
አምባ-ገነን ባህሪው ከሁለት አስርታት በላይ በስልጣን መቆየቱ የፈጠረው መሰላቸት፣ ስልታዊ የመብት ጭፍለቃ መረብ መዘርጋት፣
የመናገርና የመደራጀት ዲሞክራሲያዊ መብት በ‹‹ሕግ›› ስም ማፈን፣ የዋጋ ንረትና የስራ አጥ ቁጥር አለቅጥ ማሻቀብ (በተለይም
ከትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡት ወጣቶች ስራ-አጥ ለመሆናቸው ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ መሆኑ)፣ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ
ደግሞ በአገሪቱ አስከፊ ድህነት ማስፈኑ፣ የፍትህ እጦት፣ የፕሬስ አፈናው እንደ ‹‹ፍትህ››፣ ‹‹ፍኖተ ነፃነት››፣ ‹‹ልዕልና››፣ ‹‹ሰለፊያ››
ጋዜጦች፤ እንዲሁም ‹‹አዲስ ታይምስ›› እና ‹‹የሙስሊሞች ጉዳይ›› ያሉ መጽሔቶችን በኃይል ወደመዝጋት ከመሻገር አልፎ ተርፎ
ማህበራዊ ድረ-ገፆች፣ የአሜሪካ እና የጀርመን ድምፅ የሬዲዮ ስርጭት፣ አልጀዚራ እና ኢሳትን የመሳሰሉ ሚዲያዎችን ‹‹አመፅ ቀስቃሽ››
በሚል ውንጀላ ለማፈን በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የድሀ ሕዝብ ሃብት ማባከኑ፣ የደሞዝ ማሻሻያ አለመደረጉ፣ በተለያዩ ከተሞች
የታየው የዜጎች ከርስት መፈናቀል፣ የመሬት ቅርምት፣ እያቆጠቆጠ የነበረው የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት በ2002ቱ ምርጫ በአውራ ፓርቲ
መተካቱ፣ የሲቪክና ሙያ ማህበራት ከተፅእኖ ነፃ መሆን አለመቻል፣ የሀገሪቱ ጭቁን ወታደር ኑሮ ከእጅ ወደአፍ መሆን፣ የአርሶ አደሩም
ሆነ የከተሜው ሕይወት አለመለወጥ፣ የብሔር ጥያቄ ክሸፈት ከእርስ በእርስ ፍጥጫ ተሻግሮ በተለያዩ ክልሎች የዘውጉ ቋንቋ ተናጋሪ
ያልሆኑ ዜጎች መፈናቀል ማስከተሉ፣ የኢኮኖሚ እድገት አለመታየቱ፣ በሰላማዊ መንገድ ፍትሃዊ ጥያቄዎቻቸውን ባቀረቡ የእስልምና
እምነት ተከታዮች ላይ በአርሲ፣ በወሎ፣ በአዲስ አበባና በመሳሰሉት አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመው ሞት እና የጅምላ እስር፣
ማሕበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ እየተሞከረ ያለው ሴራ፣ የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር የፈጠረው ችግር፣ ከፖለቲካው መገልል እና መሰል
የአገዛዙ ጭካኔ ባሕርያት ስርየታቸው በሕዝባዊ አብዮት ብቻ ይሆን ዘንድ ማስገደዱን ከቶስ ቢሆን ማን ይስተዋል?!

በአናቱም የሁሉም የሥልጣን እርከን ጠቅላይ የነበረው አቶ መለስ ማለፍን ተከትሎ የተፈጠረው የመዋቅር ክፍተት ሕዝባዊ
አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ከዕዝ ውጪ ማድረጉ እና ቀድሞ በግንባሩ ውስጥ ተጨፍልቀው የነበሩ ጥያቄዎችም ሆኑ የተለያዩ
ቅሬታዎች አቧራቸውን አራግፈው ጠረጴዛው ላይ መቀመጣቸው ገፊ-ምክንያት ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒ የግንባሩ መሪዎች በደፈናው አብዮትን ከሽብር ድርጊት ጋር ቀላቅለው ከማውገዛቸው በተጨማሪ፣ የየካቲቱ
አብዮትን ጠልፎ ሥልጣን የተቆናጠጠውን የመንግስቱ ኃይለማርያምን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ለዘመን ተጋሪዎቼ በዘጋቢ ፊልም ስም እያሳዩ
አንድም ፍርሃት ለመፍጠር መሞከር፤ ሁለትም ‹‹እኛ ነን ከዚህ በላኤ-ሰብ ሥርዓት ነፃ ያወጣንህና ሃምሳ ዓመት ሰጥ-ለጥ ብለህ ተገዛ›፤
ሶስትም የቀለም አብዮትን ጭራና ቀንድ አብቅለውበት ሽብር በመንዛት ላይ ያነጣጠረ ጊዜ ያለፈበት የፖለቲካ ቁማር በመቆመር
መጠመዳቸው ከአብዮት ያነሰ አማራጭ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ በርግጥ የዴሞክራሲያዊ መብቶች እና የሕግ የበላይነት በተከበረባቸው
ሀገራት የቱንም ያህል የጠነከሩ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ቢነሱ፣ ብዙውን ጊዜ ከአብዮት ይልቅ በምርጫ ፖለቲካ ብይን ሲሰጥባቸው
የመታየቱ አጋጣሚ መዘንጋት የለበትም፡፡

የሆነው ሆኖ የድህረ-መለሱ ኢህአዴግ የፖለቲካ ማሻሻያ ከማድረግ፤ በመከላከያ ሠራዊቱ፣ በፌደራል ፖሊስ እና በደህንነት ሰራተኞቹ
ደፍጣጭነት መተማመንን መርጦ፣ ‹ነገም ዝምታው እንዳረበበ፣ አደባባዩም የፀጥታ ዳዋ እንደወረሰው፣ የእኛም መንበረ-ስልጣን
እንደተረጋጋ መሽቶ ይነጋል› በሚል ተምኔታዊ ተስፋ በመወሰዱ፣ ታሪክ ራሷ በተቃራኒው ቆማ የሶስተኛው አብዮት ሰለባ እንዲሆን
መበየኗን ለመስበክ ነብይ መሆንን አይጠይቅም (በነገራችን ላይ በሶስተኛው አብዮት ለበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች መወሳሰብና
4

አለመግባባቶች መግፍኤ የሆኑት ‹‹አሻጥራዊ የፖለቲካ ባሕል፣ የብሔር፣ የመሬት ጥያቄ እና መሰል ጭብጦች የማያዳግም ምላሽ
እንዲያገኙ ቅድመ-ዝግጅት ካልተደረገ ለአራተኛ አብዮትም መነሾ ሊሆኑ መቻላቸውን ማሳሰቡ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ)

የህዳሴ አብዮት
ከላይ የሰፈረው ሀተታ ሁላችንንም የሚያስማማ ይሆናል በሚል መተማመን በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት (ምናልባትም በቀጣዩ አዲስ
ዓመት መጀመሪያ) ሀገሬን በተቀደሰ መንፈስ ለመዋጀት የግድ መቀስቀስ ያለበት ሕዝባዊ ንቅናቄ ‹‹የህዳሴው አብዮት›› የሚል ስያሜ
ቢኖረው፣ በግሌ ለቅብሉነቱም ሆነ አንድምታውን በቀላሉ ለማብራራት የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ …ያም ሆነ ይህ በሚቀጥለው
ሳምንት ከህዳሴው አብዮት አፈፃፀም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ የመነሻ ሃሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
May 26, 2014

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: