‹‹የጠቅል አሽከር¡››

በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የንጉሡ አሽከሮች፣ ወዳጆችና፣ አድናቂዎች ‹‹የጠቅል አሽከር›› ብለው ይፎክሩ ነበር፡፡ ‹‹ጠቅል›› የዐፄ ኃይለ ሥላሴ የፈረስ ስም ነው፡፡ የጠቅል አሽከር -ማለትም የዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሽከር ብሎ እንደ መኩራራት ነው፡፡ ያ ዘመን አለፈ፡፡ ጠቅልም አሟሟታቸው በቅጡ ሳይታወቅ በደርግ ተገደሉ፡፡ የጠቅል አሽከሮች ግን መልካቸውን ቀይረው ዛሬም አሉ፡፡
ዛሬ ያሉት የጠቅል አሽከሮች ‹‹የጠቅል አሽከር›› ብለው የሚፎክሩ አይደሉም፡፡ እንዴው ዝም ብለው የሚጠቀልሉ ናቸው፡፡ አንድን ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ፣ አንድን ሀገር፣ ክልል ወይም አካባቢ እንዴው ጠቅልሎ ‹‹እንዲህ ነው እንዲያ ነው›› ብለው የሚፈርጁ ናቸው፡፡ ኦሮሞ እንዲህ ነው፣ አማራ እንዲህ ነው፣ ትግሬ እንዲህ ነው፣ ሶማሌ እንዲህ ነው፣ ሲዳማ እንዲህ ነው፣ አፋር እንዲህ ነው ብለው የሚደመድሙ ናቸው የጠቅል አሽከሮች፡፡
አንድ ሕዝብ፣ ብሔር ወይም ብሔረሰብ በውስጡ ሚሊዮን ሰዎች፣ የተለያዩ አስተሳሰቦች፣ የተለያዩ ፍላጎቶች፣ ዕውቀቶችና ለብዙ ዘመናት የተከናወኑ ለውጦች፣ የሚገኙበት የማኅበረሰብ ክፍል ነው፡፡ በርግጥ ያንን ሕዝብ አንድ ሕዝብ የሚያደርጉት የጋራ ባሕል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ የአነዋወር ዘይቤ ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም የዚያ ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባል ያንን ተቀብሎ፣ አምኖና ተግብሮ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ከዚያ ማኅበረሰብ አንዱን ወይም ሁለቱን የጋራ እሴት ብቻ ወስዶ ሌላውን ከሌላው ብሔረሰብና አካባቢ፣ አልፎ ተርፎም ከሌላ ሀገር ሕዝብ የሚወስድ፤ ጭራሽም በትውልድ የዚያ ማኅበረሰብ አባል ከመሆኑ በቀር በቋንቋ፣ በእምነት፣ በባሕል ወይም በአነዋወር ዘይቤ የማይመሳሰል ሰውም አለ፡፡
በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚወደድ፣ የሚደነቅ፣ የሚኮራበት ባሕል፣ አስተሳሰብና አነዋወር እንዳለ ሁሉ፤ የማይፈለግ፣ የሚነወርና የሚጎዳም አለ፡፡ ከማኅበረሰቡ አንዳንዱ የማይፈለገውን፣ የሚነወረውንና የሚጎዳውን ለማስቀረት ሲታገል፣ ሌላው ደግሞ ለምን ትነካብኛለህ? ብሎ የሚታገል አለ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች ተዋሕደውና ተዋውጠው ሌላ ዓይነት ማኅረሰብ ይፈጥሩና ያ የተፈጠረው ማኅረሰብ የብዙ ባሕሎች፣ አመለካከቶች፣ ቋንቋዎችና አነዋወሮች ቅይጥ የሚሆንበትም ጊዜ አለ፡፡
እንዲህ ያለውን እውነታ ድጦና ደፍጥጦ አንድን ሕዝብ ‹‹እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው›› ብሎ ደምድሞ መናገር የጠቅል አሽከር መሆን ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚናገሩ አንዳንድ እናውቃለን ባዮች ‹‹ይሄኛው ትምክህተኛ፣ ያኛው ጠባብ፣ ይኼኛው ደግሞ ገዥ፣ ያኛው ጎሰኛ፣ ይኼ ደግሞ ተገንጣይ ነው›› ብለው በድምዳሜ ይናገራሉ፡፡ ያ ማኅበረሰብ ተነጋግሮና ተስማምቶ እኔ እንዲህ ነኝ፣ ይህንን እቀበላለሁ ባላለበት ሁኔታ አንተ እንዲህ ነህ ብሎ ደምድሞ መናገር እንዴት ይቻላል?የጠቅል አሽከር ካልሆኑ በቀር፡፡
ይህ የጠቅል አሽከርነት በዕለት ተዕለት ኑሯችንም ላይ ይታያል፡፡ አበሻ ምቀኛ ነው፣ አበሻ ቀጠሮ አያከብርም፣ አበሻ ወሬኛ ነው እያሉ መደምደም ነው የጠቅል አሽከሮች አሉ፡፡ የተወሰኑ፣ የምናውቃቸው፣ ያጋጠሙን ሰዎች ምቀኛ፣ ሸረኛ፣ ቀጠሮ የማያከብሩ፣ ወሬኞች ለሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚያ ሰዎች ግን 80 ሚሊዮን ሕዝብን ወክለው ‹አበሻ› የሚያሰኙ አይደሉም፡፡ አበሾችም እነርሱ ብቻ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ሰዎችማ አንድ የሚያበሳጭ፣ የሚያስቆጣ ወይም ያልተገባ ሥራ የሚሠራ ሰው ሲያጋጥማቸው ‹አይ አበሻ› ‹ድሮስ አበሻ›› ማለት ይቀናቸዋል፡፡ ‹‹ደግሞ ለአበሻ›› ብላ ንቀውን ተጸይፈውን የደመደሙ የጠቅል አሽከሮችም ሞልተውናል፡፡ በተቃራኒውም እንዲሁ በጎ በጎ ነገሮችን ሁሉ ጠቅልለው ለፈረንጅ የሚሰጡ የጠቅል አሽከሮችም አሉ፡፡ ‹አይ ፈረንጅ› ብለው የሚፎክሩ፡፡  የፈረንጅ ምቀኛ፣ ተንኮለኛ፣ ሸረኛ፣ ጎጠኛ፣ ወሬኛ የሌለ የሚመስላቸው፡፡ ያውምኮ በቢሊዮን ከሚቆጠር ፈረንጅ ሃያ ሠላሳውን ይሆናል የሚያውቁት፡፡ ለእነርሱ ሂትለርና ሞሶሎኒ፣ ኢያጎና ሻይሎክ አበሾች ናቸው፡፡
‹አይ የዛሬ ሴት›፣ ‹አይ የዛሬ ወንድ› የሚሉ የጠቅል አሽከሮችስ አልሰማችሁም? ሁለት ሴቶች፣ አራት ወንዶች ባደረጉት ነገር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶችንና ሴቶችን የሚጠቀልሉ፡፡ አይ ነጋዴ፣ አይ ጋዜጠኛ፣ አይ ቀበሌ፣ አይ ወረዳ፣ አይ ሐኪም፣ አይ  ታክሲ፣ አይ ወያላ፣ አይ የዛሬ ተማሪ፣ አይ ሆስተስ፣ እያሉ የሚጠቀልሉስ፡፡ ምንም ያህል አብዛኞቹ በችግር ውስጥ ቢነከሩ፣ በሥነ ምግባር ድቀት ቢዳክሩ፣ በግል ጥቅም ቢታወሩ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለዘር የሚተርፉ አሉ፡፡ የጠቅል አሽከርነት ግን ለእነዚህ ለትሩፋን ቦታ የለውም፡፡ የጠቅል አሽከርነት ካልጠቀለለ ነጥሎም አንጥሮም ማየት አይቻለውም፡፡
ያለፈው ታሪካችን ሁሉ አስከፊ፣ አስጸያፊ፣ አንገት አስደፊ ነው ብለው የሚደመድሙ፤ የቆየ ነገር ሁሉ ኋላ ቀር፣ ጎታችና ለዕድገት ፀር የሚመስላቸው፤ የእነርሱ አያቶች ሲዋጉና ሲራቡ ብቻ የኖሩ አድርገው የሚገምቱ የጠቅል አሽከሮች እንዳሉት ሁሉ የቀድሞው ነገር ሁሉ ምርጥ፣ ልዩ፣ ሊነካ የማይገባው፣ እንዳለ መጠበቅ የሚገባው፣ እንከን የማይወጣለት አድርገው የሚፎክሩ የጠቅል አሽከሮችም አሉ፡፡
ለእነዚህ የጠቅል አሽከሮች በንጉሡ ዘመንና በደርግ ዘመን ምንም ዓይነት በጎ ሥራ አልተሠራም፡፡ ለእነርሱ ዋናው ጉዳይ ሥራው ሳይሆን የተሠራበት ዘመን ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ሥርዓቶች ሰው ሲገደል፣ ሲጨቆን፣ ሲራብ፣ ሲገፋ፣ ሲሰደድ፣ ብቻ ነው የነበረው፡፡ ሌላ ነገር አልነበረም፤ ሌላ ነገር አልተሠራም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሁን ባለንበት ዘመን ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር የለም፤ ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ነው፡፡ ዛሬ ሁሉ ደልቶት፣ ሁሉ ተመችቶት ነው የሚኖረው፡፡ ለዚያኛው ሙሉ ጥላቻ፣ ለዚህኛውም ሙሉ ፍቅር አላቸው፡፡ ያኛው ፍጹም ሰይጣን፣ ይኼኛውም ፍጹም መልአክ ነው፡፡
በአንድ በኩል የፕላቶ የአሪስቶትልና የሶቅራጥስና የስክንድስ ፍልስፍና፣ የእስክንድር ታሪክ፣ የበርለዓም የሕንድ መጽሐፍ፣ የዮሐንስ መደብር የዓለም ታሪክ፣ ፈውስ ሥጋዊን የመሰለ የሕክምና መጽሐፍ መኖራቸውን ዘንግተው በግእዝ የተጻፈው ሁሉ ሃይማኖታዊ፣ ቅዱስና ለጽድቅ ብቻ የተጻፈ የሚመስላቸው የጠቅል አሽከሮች እንዳሉት ሁሉ፤ እንድ እና ሁለት መጻሕፍትን ብቻ ተመልክተው በግእዝ የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ ከሃይማኖት ያለፈ ፋይዳ የሌላቸው አድርገው የሚደመድሙ የጠቅል አሽከሮችም ሞልተዋል፡፡
የአማርኛ መጽሐፍ አላነብም፣ የአማርኛ ፊልም አላይም፣ የአማርኛ ዜና አልሰማም የሚሉ የጠቅል አሽከሮች፡፡ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ሁሉ ዕውቀትና ብልሃት የሚመስላቸው፡፡ የዚህ ሀገር ልብስ፣ የዚህ ሀገር ጫማ፣ የዚህ ሀገር ቦርሳ፣ የዚህ ሀገር ዕቃ፣ የዚህ ሀገር ሁሉ ቀሽም ነው ብለው የደመደሙ የጠቅል አሽከሮች – እዚህ፣ እዚያ እዚያ ማዶም አሉ፡፡
መጠቅለል ልዩ ነገርን እንዳናይ ይጋርዳል፡፡ ከመቶዎች ውስጥ ልዩ ለሆነው አንድ ሰው ዕድል እንዳያገኝ ያግዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለመታየትና ለመሰማት ዕድል ባላቸው ጥቂት አካላት ምክንያትም የመጡበትን አካባቢ፣ ማኅበረሰብና ሙያ ደምድመን እንድንናገርም ያደርገናል፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ የተለየ ነገር መሥራት፣ የተለየ ጠባይ መላበስ፣ የተለየ አመለካከት መያዝ፣ የተለየ አነዋወር መኖር የሚፈልግ ሰው ከተጠቀለሉት ነጥሎ የሚቀበለው ስለማይኖር በጠቅል አሽከሮች ተደፍቆ ይቀራል፡፡ ብዙ ሰው የተናገረለት ነገር ደግሞ ሰነባብቶ እማሬ ይሆናል፡፡ ከዚያም ያንን ማስተባበል ይከብዳል፡፡አንድ እግረኛ ያወራውን ሃምሳ ፈረሰኛ አይመልሰውም ይባላልና፡፡ እኛ ግን ለራሳችን  እንዲህ እንበል ‹የጠቅል አሽከር አይደለሁም››፡፡ እነዚህንም  ያለ መረጃና፣ ያለ ማስረጃ፣ ያለ ዳታና ያለ ይሉኝታ እየጠቀለሉ የሚናገሩትን ‹‹የጠቅል አሽከር›› እንበላቸው፡፡ እንዴው ቢታረሙ፡
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: